Loading......
template-img

የመሸሸግ ወንጀል ምንነትና የሕግ ተጠያቂነት

​በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 682 (1) መሰረት የመሸሸግ ወንጀል የሚባለው አንድ ንብረት እንደ ስርቆት፣ ውንብድና፣ ማታለል ወይም ዘረፋ ባሉ በንብረት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የተገኘ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባ፣ ያንን ንብረት በግዢ፣ በተውሶ፣ በስጦታ፣ በመያዣነት ወይም በማናቸውም በሌላ መንገድ መረከብ፣ መጠቀም፣ ማስቀመጥ፣ መደበቅ ወይም ለሌላ ሰው አሳልፎ መሸጥ እንዲሁም በመሸጥና በመለወጥ ሂደት ውስጥ በአገናኝነት መርዳት ነው። ይህ ድርጊት እንደ ወንጀሉ ክብደት በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በመቀጮ ያስቀጣል። ​በሕጉ አገላለጽ የመሸሸግ ወንጀል በቸልተኝነት ቢፈጸም እንኳ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑ በአንቀጽ 682 (3) ላይ በግልጽ ተደንግጓል። አንድ ሰው ዕቃው የወንጀል ውጤት መሆኑን በእርግጠኝነት ባያውቅም፣ ነገር ግን ሁኔታዎቹን አመዛዝኖ ይህ ዕቃ በሕገወጥ መንገድ የመጣ ሊሆን ይችላል ብሎ ለመጠራጠር የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች እያሉ ጥንቃቄ ሳያደርግ ሲቀር በቸልተኝነት መሸሸግ ይባላል። ለዚህም እንደ ማሳያ የንብረቱ ዋጋ ከገበያ ዋጋው እጅግ በጣም ያነሰ ሆኖ መገኘት፣ የሻጩ ሁኔታ አጠራጣሪ መሆን ወይም ድርጊቱ የሚፈጸምበት ቦታና ሰዓት ከተለመደ ውጪ መሆን፣ እንዲሁም እንደ ሞባይል ያሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የይለፍ ቃል ያልተከፈተላቸው መሆኑ ቸልተኝነትን ሊያሳዩ ከሚችሉ በርካታ ነጥቦች ውስጥ ናቸው። ለምሳሌ ዋጋው 70,000 ብር የሚሆን ዘመናዊ ስልክ መንገድ ላይ በ5,000 ብር ሲሸጥ ለምን ይሄን ያህል ረከሰ ብሎ አለመጠየቅ ቸልተኝነትን ሊያሳይ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ዕቃውን የሚሸጠው ሰው ስለ ዕቃው በቂ እውቀት የሌለው መሆኑ፣ ወይም ዕቃውን በድብቅና አጠራጣሪ በሆነ ቦታ ለምሳሌ በድብቅ ስፍራ ወይም በጨለማ ለመሸጥ መሞከሩ እንዲሁም የሞባይል ስልኩ መቆለፊያ ያልተከፈተ መሆኑና የቀድሞ ባለቤት መረጃዎች በውስጡ መኖራቸው ቸልተኝነትን ሊያሳዩ ይችላሉ።

በእነዚህና መሰል ሁኔታዎች ላይ ተገቢውን ማጣራት ሳያደርጉ ድርጊቱ በቸልተኝነት የተፈጸመ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፣ ግለሰቡ ዕቃው በወንጀል የተገኘ መሆኑን እያወቀ ወድዶና ፈቅዶ ከፈጸመው ግን ሆነ ተብሎ በተፈጸመ የመሸሸግ ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል። ወንጀሉ ይበልጥ ከባድ ሆኖ የሚታየው ድርጊቱ የተፈጸመው በሰዎች ወይም በንብረት ላይ ወንጀል ለመፈጸም በተቋቋመ ቡድን አባልነት ከሆነ፣ የሥራ ወይም የንግድ ፈቃድን ለዚሁ ተግባር በመጠቀም ከሆነ፣ ወይም ንብረቱ የተገኘው በውንብድና፣ በዘረፋ፣ በባሕር ላይ ውንብድና ወይም የመንግሥት ወይም የመከላከያ ሠራዊት ንብረት መሆኑን እያወቁ ከሆነ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 683 መሰረት በከባድ የመሸሸግ ወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል። የዚህም ቅጣት እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ 20,000 ብር የገንዘብ መቀጮ ሊደርስ ይችላል። ስለሆነም ማንኛውም ሰው ንብረት በሆነ መንገድ ወደ እጁ ሲገባ የመጣበትን መንገድና ሕጋዊነት የመመርመር ግዴታ አለበት። ይህ ካልሆነ ግን የወንጀል ፍሬ የሆነን ንብረት በመያዝ፣ በመደበቅ ወይም በማስተላለፍ ተጠያቂነት ሊመጣ ይችላል። በመሆኑም ከሕግ ተጠያቂነት ለመዳን ማንኛውንም ግብይት ወይም ርክክብ በሕጋዊ ሱቆችና የንግድ ማዕከላት በኩል ማከናወን፣ ደረሰኞችንና የባለቤትነት ማረጋገጫዎችን መጠየቅ እንዲሁም አድራሻቸው ካልታወቁ ግለሰቦች ጋር ከሚደረግ አጠራጣሪ ግንኙነት መቆጠብ ብልህነት ነው። ጥንቃቄ ይደረግ ለማለት ነው።

Previous Post Next Post

(0) comments to this article

No Reviews

Leave a reply