ፍርድ ያረፈበት ጉዳይ (Res Judicata)፡ ፍርድ ቤቶች መቃወሚያ ሳይቀርብላቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ክስን ውድቅ ማድረግ ይችላሉን?
የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 5 (1) በማንኛውም ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ፣ በዚያው የክርክር ሥረ-ነገር እና ጭብጥ ላይ፣ በነበሩት ተከራካሪዎች ወይም ከተከራካሪዎቹ መብት ባገኙ ሦስተኛ ወገኖች መካከል በድጋሚ ክስ ሊቀርብ እንደማይችል ይደነግጋል። የዚህ ድንጋጌ ዋነኛ ዓላማ ለአንድ ክርክር ዘላቂ መደምደሚያ በመስጠት የሕግ የበላይነትን እና የፍርዶችን ተፈጻሚነት ማረጋገጥ ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህ ድንጋጌ በተግባር ሲተርጎም አንድ አከራካሪ ጥያቄ ያስነሳል። ተከሳሽ ሳይቀርብ ቀርቶ ጉዳዩ በሌለበት በሚታይበት ወቅት ወይም ተከሳሽ ቀርቦ "ፍርድ ያረፈበት ጉዳይ" (Res Judicata) የሚል መቃወሚያ ባላነሳበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ክሱ ቀደም ሲል ውሳኔ ያገኘ መሆኑን በራሱ ካወቀ ክሱን ውድቅ ማድረግ ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ! በአንድ በኩል፣ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 244 (2)(ረ) እና (3) መሠረት፣ ፍርድ ያረፈበት ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ሊቀርብ የሚገባ ሲሆን፣ ተከራካሪ ወገን ክስ ከመሰማቱ በፊት በመጀመሪያው ዕድል መቃወሚያውን ካላቀረበ መብቱን ሆን ብሎ እንደተወ (Waiver) ይቆጠራል የሚል ሀሳብ ሊቀርብ ይችላል። ፕሮፌሰር አለን ሴድለር ‘የኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ማብራሪያ’ በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ጉዳዩ የዳኝነት ሥልጣን (Jurisdiction) ጥያቄ ባለመሆኑ፣ ተከራካሪዎች ካላነሱት ፍርድ ቤቱ አልፎት ሊሄድ እንደሚገባ ይከራከራሉ። በሌላ በኩል፣ ቀደም ሲል ውሳኔ ያገኘ ጉዳይን በድጋሚ ማየት የፍትሕ ሥርዓቱን አስተማማኝነት የሚሸረሽር፣ ለተጣረሱ ውሳኔዎች በር የሚከፍት እና የባለጉዳዮችን ጊዜና ሀብት ያለአግባብ የሚያባክን ተግባር በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት በድጋሚ የቀረበውን ክስ ውድቅ ሊያደርገው ይገባል የሚል ጠንካራ ሞገት ይቀርባል።
ይህንን የሕግ ክርክር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 25፣ በሰ/መ/ቁጥር 182044 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እልባት ሰጥቶታል። ችሎቱ እንዳመለከተው ተከሳሽ ባይቀርብም ወይም ቀርቦ መቃወሚያ ባያነሳም፣ ፍርድ ቤቱ ክሱ ቀደም ሲል ፍርድ ያገኘ መሆኑን ከተረዳ በራሱ ተነሳሽነት ውድቅ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም፣ በሕግ ስልጣን በተሰጠው ፍ/ቤት ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ ላይ ድጋሚ ክስ መቅረቡ የተከራካሪ ወገኖችን ጊዜ የሚያባክን፣ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ፣ ጉዳዮች ፍጻሜ እንዳያገኙ የሚያደርግ እና በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የተጣረሰ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችልበትን እድል የሚፈጥር በመሆኑ፡፡ ስለሆነም፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሚሰጠው የሕግ ትርጉም ካለው አስገዳጅነት ባህሪ የተነሳ ፍ/ቤቶች ከሳሽ ያቀረበው ክስ አስቀድሞ ፍርድ ባገኘ ጉዳይ ላይ መሆኑን በራሳቸው በተረዱ ጊዜ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 5 እና 244 (3) መሰረት ክሱን ውድቅ ሊያደርጉት ይገባል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

(0) comments to this article
No Reviews