Loading......
template-img

ስለ ሙከራ ጊዜ (Probation Period) ቅጥር ማወቅ ያለብን ወሳኝ ነጥቦች (By Jura Legal Update)

​ለሠራተኛውም ሆነ ለቀጣሪው ግልጽ የሆነ መረጃ መኖሩ አላስፈላጊ አለመግባባቶችን ይቀንሳል። በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሠረት የሙከራ ጊዜ ስምምነት በጽሁፍ መደረግ ያለበት ሲሆን፣ የሙከራ ጊዜውም ከ 60 የሥራ ቀናት ሊበልጥ አይችልም። ሠራተኛው ቀድሞ ይሠራው በነበረ ሥራ ላይ እንደገና በአሠሪው ቢቀጠር ለሙከራ ጊዜ ሊመደብ አይችልም። አሰሪው፣ ሠራተኛው ለሥራው ተስማሚ አለመሆኑ ሲረጋገጥ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ የስንብት ክፍያና ካሣ መክፈል ሳይገደድ ውሉን ማቋረጥ ይችላል። በተመሳሳይ ሠራተኛውም ያለ ማስጠንቀቂያ ሥራውን የመልቀቅ መብት አለው። በነገራችን ላይ፣ አሠሪው ለሙከራ የተቀጠረን ሠራተኛ ለሥራው ተስማሚ መሆኑን ሳይመዝን (ሳይገመግም) ማሰናበት አይችልም። ይህ ካልተደረገ ስንብቱ ሕገ-ወጥ ይሆናል። ​የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 212420 በሰጠው ውሳኔ፣ አሠሪው ሠራተኛውን ለታቀደለት ቦታ ተስማሚ መሆኑን ሳይመዝን ካሰናበተ ሠራተኛው የሙከራ ጊዜውን ቢጨርስ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ደመወዝ ካሣ የማግኘት መብት ይኖረዋል።

አሠሪው ሠራተኛው ለሥራው ተስማሚ አለመሆኑን በተጨባጭ ሳይመዝን (ሳይገመግም) ካሰናበተ፣ ስንብቱ ሕገ-ወጥ ስንብት ተብሎ ይፈረጃል። በሙከራ ጊዜ ላይ ያለ ሠራተኛም ቢሆን ያለ ግምገማ መባረር የለበትም የሚል ጥበቃ ያደርጋል። ስንብቱ ሕገ-ወጥ ሆኖ ሲገኝ ሠራተኛው የካሣ መብት ይኖረዋል። ሆኖም ካሣው የሚሰላው መደበኛ ሠራተኛ እንደሚሰላው ሳይሆን ​ሠራተኛው የሙከራ ጊዜውን ቢጨርስ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ደመወዝ ታሳቢ በማድረግ ነው። ​በዚህም መሠረት የሙከራ ጊዜው 60 ቀናት (2 ወር) ስለሆነ፣ ሠራተኛው ሊያገኝ የሚችለው ከፍተኛው የካሣ መጠን የ2 ወር ደመወዝ ብቻ ነው። ሆኖም ግን፣ ሠራተኛው በሙከራ ላይ ያለ በመሆኑና ገና ቋሚ አገልግሎት ስላልጀመረ የሥራ ስንብት (Severance Pay) እና ​የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያዎች አይከፈሉትም። ​ ሌላው፣ በሕግ፣ በሕብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ በሌላ አኳኋን ካልተደነገገ በስተቀር በሙከራ ላይ ያለ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሌላ ሠራተኛ ያለው መብትና ግዴታ ይኖረዋል።

Previous Post Next Post

(0) comments to this article

No Reviews

Leave a reply