Loading......
template-img

የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ አጭር ዳሰሳ

በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዙ ግብይቶች እና የመንግስት አገልግሎቶች ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ መሰረት የጣለው የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚደረጉ መልዕክቶች እና ዲጂታል ፊርማዎች እንደ ወረቀት ሰነድ ተቆጥረው ሕጋዊ ውጤት እንዲኖራቸው ይፈቅዳል። ይህ አዋጅ ከመጽደቁ ቀደም ብሎ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ለዲጂታል መለያና ለማረጋገጫ ሥርዓት ቴክኒካዊ መሠረት ጥሎ የነበረ ቢሆንም፣ አዋጅ ቁጥር 1205/2012 ግን የዲጂታል ግብይቶችን አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው አድርጎታል። የፊርማ አዋጁ የአንድን አካል ማንነት በማረጋገጥ ላይ ትኩረት ሲያደርግ፣ የትራንዛክሽን አዋጁ ደግሞ ያ ፊርማ የሚያርፍበትን ግብይት፣ የኢ-ኮሜርስ ሥርዓት እና የሸማቾችን መብት ሕጋዊ ውጤት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ምሰሶ ነው። አዋጁ የኤሌክትሮኒክ ንግድ (E-Commerce) እውቅና በመስጠት በዚህ ለሚገበያዩ ሸማቾች ጥበቃ ያደርጋል። ነጋዴዎች ስለሚሸጡት እቃ ትክክለኛ መረጃ የመስጠት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የክፍያ ስርዓት የመዘርጋት ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ሆኖም ግን፣ አዋጁ ማንም ሰው በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲገበያይ ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ አያስገድድም። ማንኛውም ግለሰብ በዲጂታል መንገድ ለመገበያየት ወይም አገልግሎት ለማግኘት ካልፈለገ በስተቀር በዚህ ሥርዓት እንዲጠቀም አይገደድም። ​ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ ተፈጻሚ የማይሆንባቸው ልዩ ጉዳዮችን በግልጽ ለይቶ አስቀምጧል። አዋጁ ለዲጂታል አሰራር በር ቢከፍትም፣ ለአንዳንድ ጉዳዮች ግን አሁንም በወረቀት እና በአካል መገኘትን የግድ ይላል። የሚከተሉት ጉዳዮች በኤሌክትሮኒክ መንገድ ብቻ ሊከናወኑ እንደማይችሉ አዋጁ ይገልጻል። በአዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (2) ላይ እንደተገለጸው፣ አዋጁ ተፈጻሚ የማይሆንባቸው ወይም በኤሌክትሮኒክ መንገድ ሊከናወኑ የማይችሉ ልዩ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦ ​ሀ) ጋብቻን እና ፍቺን ጨምሮ ከግል ሁኔታ (Personal Status) ጋር የተያያዙ ማናቸውም ጉዳዮች፤ ​ለ) ከኑዛዜ መስጠት፣ ከኑዛዜ ፎርሞች፣ ኑዛዜን ከመሻር እና ከውርስ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፤ ​ሐ) የፍርድ ቤት ትዕዛዞች፣ መጥሪያዎች (Summons)፣ የብርበራና የመያዣ ትዕዛዞች፣ የእስር ማዘዣዎች እና ሌሎች የፍርድ ቤት ውሳኔዎች፤ ​መ) በማይንቀሳቀስ ንብረት (Immovable Property) ላይ ያለን ማንኛውንም መብት ወይም ጥቅም ከማስተላለፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፤ እና ​ሠ) ከሕጋዊ የውክልና ጉዳዮች (Power of Attorney) ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው።

እነዚህ ጉዳዮች በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ወይም በዲጂታል ፊርማ ብቻ ሊከናወኑ አይችሉም። እነዚህ ጉዳዮች ከአዋጁ ተፈጻሚነት ውጭ የተደረጉት በዋነኝነት ለጥንቃቄ ይመስላል። ጉዳዮቹ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውጤት የሚያስከትሉ በመሆናቸው፣ ግለሰቦች በአካል ቀርበው እንዲፈርሙ ማድረጉ ውሳኔው በስሜት ወይም በቸልተኝነት ሳይሆን ቆም ብሎ በማሰብ እንዲከናወን ይረዳል። በተጨማሪም በአካል መገኘት እንደ ማስገደድ ወይም ማጭበርበር ያሉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና የፈራሚውን ማንነት እንዲሁም የአእምሮ ጤንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ከመረጃ ደህንነት እና አስተማማኝነት አንጻርም ሲታይ፣ እንደ ኑዛዜ እና የቤት ሽያጭ ያሉ ሰነዶች ለረጅም አስርት ዓመታት ተጠብቀው መቆየት ያለባቸው በመሆናቸው፣ በዲጂታል ሥርዓት ላይ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ የቴክኖሎጂ መቋረጦች ወይም የሳይበር ጥቃቶች ስጋት ነጻ ለመሆን የወረቀት ሰነድ አስፈላጊነት የቀጠለ ይመስላል። ከዚህም ባሻገር፣ የፍትሐብሔር ሕግ ለነዚህ ጉዳዮች ጥብቅ የሆኑ ፎርማሊቲዎችን ያስቀምጣል። ለምሳሌ ኑዛዜ በምስክሮች ፊት መደረግ አለበት፣ የቤት ሽያጭ ውል ደግሞ መመዝገብ አለበት ይላል። የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጁ እነዚህን ነባር እና መሰረታዊ የሕግ ሥርዓቶች በድንገት እንዳያናጋቸው በማሰብና የሀገሪቱ የመረጃ ደህንነት (Cybersecurity) አቅም ጋር ለማጣጣም የወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ ይመስላል።

Previous Post Next Post

(0) comments to this article

No Reviews

Leave a reply