Loading......
template-img

የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የሥራ መሪ ነው ሊባል ይችላል ወይስ አይችልም?

የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የሥራ መሪ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጥያቄ እጅግ መሠረታዊና በሕግ ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው። አንድን ሠራተኛ የሥራ መሪ ነው ወይስ አይደለም ብሎ መለየት የሚያስከትለው ውጤት ግለሰቡ የሚተዳደርበትን የሕግ ማዕቀፍ የሚወስን በመሆኑ ጥያቄው ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋል። አንድ ሠራተኛ በሕጉ ትርጉም መሠረት የሥራ መሪ ሆኖ ከተገኘ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ሥር የሚገኙትን ጥበቃዎችና መብቶች በቀጥታ አያገኝም። ይልቁንም የሥራ መሪውና የአሠሪው ግንኙነት የሚመራው በሁለቱ መካከል በሚደረግ የሥራ ውል፣ በተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ ወይም እነዚህ በሌሉበት በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ ስለ ሥራ ውል በተቀመጡት አጠቃላይ ድንጋጌዎች መሠረት ብቻ ይሆናል። አሠሪና ሠራተኛ አዋጁ በሥራ መሪ ላይ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው በተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ ሲኖር ወይም ውሉ ወደ አዋጁ ሲያመለክት ብቻ በመሆኑ፣ የሥራ ድርሻን በትክክል መለየት የሕግ ከለላውን ዓይነት የሚወስን ወሳኝ እርምጃ ነው። ይህንን ጥያቄ በሚመለከት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 209295 (ቅጽ 27) ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል።

ችሎቱ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 2(10) መሠረት አንድ ሠራተኛ የሥራ መሪ ነው ሊባል የሚችለው የሥራ አመራር ፖሊሲዎችን የሚያወጣና የሚያስፈጽም፣ ወይም ሠራተኛን የመቅጠርና የማሰናበት የውሳኔ እርምጃ የመውሰድ ተግባራትን የሚያከናውን መሆኑ በማስረጃ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ገልጿል። በመሆኑም አንድ ግለሰብ የ3ኛ ደረጃ የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ቢሆንም እንኳ፣ በሕጉ የተዘረዘሩትን የሥራ መሪነት ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል የመወሰን ሥልጣን በባንኩ መዋቅር ውስጥ በግልጽ ካልተሰጠው በስተቀር የሥራ መሪ ሊባል አይችልም። ችሎቱ አፅንዖት ሰጥቶ እንዳመለከተው፣ "ሥራ አስኪያጅ" የሚል ስያሜ መያዝ ብቻውን አንድን ሠራተኛ የሥራ መሪ አያደርገውም፤ ምክንያቱም ዋናው መስፈርት መሆን ያለበት ግለሰቡ በተጨባጭ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። የባንክ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የማቀድ፣ የመወሰን፣ ሠራተኛ የመቅጠርም ሆነ የማሰናበት ተግባራት በበላይ አካላት ወይም በዋናው መሥሪያ ቤት የሚወሰኑ ሆነው ሳለ፣ በአንድ ቅርንጫፍ ውስጥ ዕለት ከዕለት በሚከናወኑ አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ ብቻ ተገድቦ የሚሠራ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በሕጉ ፊት እንደማንኛውም ሠራተኛ እንጂ እንደ ሥራ መሪ አይታይም። ይህ የሕግ ትርጉም በስያሜ ብቻ መብታቸው ተገድቦ የቆዩ በርካታ የባንክና የሌሎች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ የሚሰጣቸውን መብቶችና የሕግ ከለላዎች እንዲጠይቁ ሰፊ በር የሚከፍት ነው። የሥራ መሪነት መለኪያው የሥራው መጠሪያ ሳይሆን ግለሰቡ በተጨባጭ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት ይገባል።

Previous Post Next Post

(0) comments to this article

No Reviews

Leave a reply